የትግራይ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል በወቅታዊ ጉዳይ ላይ አስመልክተው ያስተላለፉት መልእክት ********
“አሁን ከፊት ለፊታችን ያለው ብቸኛ አማራጭ የሰላም ጥሪ የረገጠው ፋሽስታዊ ቡድንን በመደምሰስ ህዝባዊ ምከታችን በአንፀባራቂ ድል ማጠናቀቅ ብቻ ነው!” --- የትግራይ ህዝብ በረጅም የታሪክና የነፃነት ገድል ታሪኩ ህልውናውንና ደህንነቱን ከማስከበር፣ ታሪኩንና ማንነቱን ጠብቆ ከማቆየትና እንደዚሁም የግዛት አንድነቱን ከማረጋገጥ፣ ከድህነትና ኋላቀርነት አረንቋ ለመላቀቅ ተገዶ የገባበት ካልሆነ በቀር፤ የሌሎች ህዝቦች መብት ለመርገጥ አልያም ለመውረር ዓልሞ ያካሄደው ጦርነት ፈፅሞ አልነበረም። ስለሆነም የትግራይ ህዝብ በራሱ ላይ በተፈፀሙበት ቀጣይ ወረራዎች ምክንያት በየምዕራፉ ለህልውናው፣ ለመብቱና ለማንነቱ ሲል ተወዳዳሪ የሌለው ትግል አካሂዷል። በአካሄደው መራራ ትግልና በከፈለው ከባድ መስዋእትነት ደግሞ ለማንም ሳይንበረከክ ታሪኩ፣ ክብሩና ማንነቱ ሳይበረዝ ጠብቆ እንደቆየ ሁሉ ዛሬም ነፃነቱንና ክብሩን አስጠብቆ መቀጠል ችሏል። ማንነቱንና ታሪኩን ለማስቀጠል የቻለው ደግሞ በቀና ጎዳና ላይ ተጉዞ ሳይሆን እጅግ ከባድ፣ መራራና ፈታኝ መድረኮች፣ አያሌ ውስብስብ ችግሮችን በጥበብ፣ በጥንቃቄና በብቃት መሻገር በመቻሉና እያንዳንዱ ትውልድም በራሱ የግዜ መዋዕል መድረኩ የሚጠይቀውን ሁሉም ዓይነት ትግልና መስዋእትነት ስለከፈለ ነው። በአሁኑ መድረክም ቢሆን ጠላቶቻችን ካለፉት ግዜያቶች በከፋ ደረጃ የትግራይ ህዝብን ተረት ለማድረግ ማለቂያ የሌለው ኮተትና የጥፋት ግብረ-አበሮቻቸውን አሰልፈው ዳግመኛ ግልፅ ወረራ ፈፅመውብናል። ይሁን እንጂ ጠላቶቻችን እንደ ህዝብ ከምድረ ገፅ ሊያጠፉን ቢዘምቱብንም እንደ ህዝብ አንድነታችንን አጠናክረን በላቀ ፅናትና ብሄራዊ ስሜት በመታገላችን እነሆ ሁሉንም ከበባዎችን በርግደን በመጣስ የጠላቶቻችን ዕድሜ ለማሳጠርና ለአንዴና ለመጨረሻ ግዜ ለመቅበር በምንችልበት ደረጃ ላይ ደርሰናል። ስለሆነም በአሁኑ ሰዓት የትግራይ ህዝብን ዘላቂ ህልውናና ደህንነት በአስተማማኝ ደረጃ ለማረጋገጥና በጠንካራ መሰረት ላይ ለመገንባት በምንችልበት ደረጃ ላይ እንገኛለን። አሁን የትግራይ ሰራዊትን ግስጋሴ ሊያስቆም የሚችል ምድራዊ ሃይል የለም። አሁን በትግራይ ላይ ያንዣበበው የጥፋት ዳመና ለአንዴና ለመጨረሻ ግዜ ተገፎ ወደ አዲስና የተለየ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ሰፊ ዕድል ጋህድ እየሆነ ይገኛል። ተወዳዳሪ በሌለው የትውልድ ትግልና መስዋእትነት የተረከብናት ትግራይ ወገባችንን ጠበቅ አድርገን በመታገል ሁሉንም ወራሪዎች በበቃኝ ዘርረን በመቅበር እኛም እንዳለፉት ትውልዶች ሁሉ ወደ ቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ ታሪካዊ ሃላፊነት በትከሻችን ላይ ወድቋል። የዚህ ትውልድም በትከሻው ላይ ያረፈውን ሓላፊነት በላቀ ጀግንነት፣ ቆራጥነትና ክብር የትግራይ ግዛት አንድነትን በማስጠበቅ ወደ ቀጣይ ትውልዶች እንደሚያሸጋግር ለአፍታም ቢሆን አያጠራጥርም። በዚህ ወቅት ያለው ትውልድ ትግራይንና ህዝቧን ለገበያ ድርድር ማቅረብ ማሰብን ይቅርና ህልም ማለምም የሚቻል አይደለም። በትግል ዘመን መዋእሉ ለፍትሕና አንድነት የታገለው የትግራይ ህዝብ የሰላም ጣዕምና ውድ ዋጋ ከሱ በላይ የሚያውቀውና የሚፈልገው አካል ከቶ ሊኖር አይችልም። በትግራይ ህዝብና መንግስት ላይ ሊፈፀምባቸው የማይፈልጉትን ግፍና በደል በሌሎች ህዝቦች ላይም ሊደርስባቸው አይመኙም። ይሁን እንጂ በሰፊው ህዝባችን ላይ በተለይ ደግሞ በትግራይ ሴቶች ላይ የተፈፀሙ ማለቂያ የሌለው ግፍና በደሎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የተሳተፉ አካላት ሁሉ በገቡበት ገብተን ፍርዳቸውን እንዲያገኙ ማደረጋችን የግድ ይላል። የትግራይ ህዝብ እንደ ህዝብ ከምደረ ገፅ ለማጥፋት በታወጀው ጆኖሳይድ የተሳተፉት ሁሉ የእጃቸውን እንደሚያገኙ ሊታወቅ ይገባል። በዚህ ላይ “ይቅር” የሚባል ነገር ሊኖር ፈፅሞ አይችልም። በአሁኑ ወቅት ወራሪ ሃይሎች የመፈፀም ዓቅማቸው ዝቅተኛ ደረጃ የወረደበት፣ የወራሪ ሃይሎች ፉከራና ማስፈራሪያ ሁሉ መሬት የመንካት ዕድሎች የሰፉበት ከመሆኑም ባሻገር ከሁሉም በላይ ህዝባዊ ሰራዊታችን የመፈፀም ዓቅሙ እጅግ በላቀ ከፍታ ደረጃ ላይ ደርሷል ማለት ይቻላል። በዚህ ሰዓት ላይ የህዝባችንን ህልውናና ደህንነት በአስተማማኝ አገባብ ለማስጠበቅ ብቻ ሳይሆን ትግራይ ዳግመኛ ልትደፈር ወደማትችልበት ደረጃ ላይ ለማሸጋገር የሚያስችል ተጨባጭ ችሎታ እንዳለን ለወዳጅም ለጠላትም ከወዲሁ ለማሳወቅ እንወዳለን። በመሆኑም አሁን ፊት ለፊታችን ላይ ያለው ብቸኛ አማራጭ የሰላም ጥሪ የረገጠው ፋሽሽታዊ ብዱንን በመደምሰስ ህዝባዊ ምክታችንን በአንፀባራቂ ድል እንዲጠናቀቅ ማድረግ ብቻ መሆኑ ታውቆ እያንዳንዱ ትግራዋይ ዜግነታዊ ግዴታውን እንዲፈፅም ጥሪየን አቀርባለሁ። ዘልአለማዊ ክብርና ሞገስ ለጀግኖች የትግራይ ሰማእታት!
ሰላም! #ትግራይ_ትስዕር